|
ንቅናቄው ለአባላቱ በምርጫ ስነ ምግባር ደንብ ስልጠና መስጠት ጀመረ
|
|
የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብአዴን አባላቱ የምርጫ ስነ ምግባር ደንቡን አክብረው እንዲያስከብሩ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡
የስልጠናው አላማ በፓርቲዎች የወጣውንና ህግ ሆኖ የፀደቀውን የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ አባላቱ ግንዛቤ ኑሮአቸው አክብረው እንዲያስከብሩት መሆኑ ተብራርቷል፡፡ የባህር ዳሩን መድረክ የመሩት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት ኢህአዴግ ገዥ ፓርቲ እንደ መሆኑ አባላቱ ይህንን ምርጫ በማክበርና በማስከበር ምርጫውን ፍትሐዊ ዲሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ይሁንታን ያተረፈ እንዲሆን ማድረግ ይገባቸዋል፡፡
የስነ ምግባር ደንቡ መውጣት ከዚህ በፊት የነበረውን ተራ መዘላለፍ የሚያስቀር፣ በብጥብጥ ወደ ስልጣን ለመውጣት የሚደረግ ሙከራን የሚከላከል በመሆኑ የሠለጠነ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የስልጣን ሽግግር በሀገራችን ለማስፈን ፋይዳው የጐላ መሆኑ ተብራርቷል፡፡ይህ ደግሞ ኢህአዲግና የኢትዮጵያ ህዝብ ሲመኙት የነበረ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የድርጅቱ አባላት ተግተው እንዲሠሩ በስልጠናው ላይ ተገልጿል፡፡
ከ6ዐ በላይ የሚሆኑት የሀገሪቱ ፓርቲዎች ይህንን የስነ ምግባር ደንብ ተስማምተውና ፈርመው ህግ ሆኖ እንዲወጣ ያደረጉ ቢሆንም ያልፈረሙና ብጥብጥን የሚሹ ሊኖሩ ስለሚችሉ ይህንን የማይፈልግ ህዝብ ለመፍጠር አባላቱ ተግተው እንዲሠሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገልፀዋል፡፡
የስነ ምግባር ደንቡን ከፈረሙት ፓርቲዎተ ጋር ችግሮች እንዳይፈጠሩ መጣርና ሲፈጠሩም በመመካከርና በመወያየት መፍታት አስፈላጊ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡
የዚህ ህግ ፋይዳ ሠውን ሲያጠፋ ማሰር ሳይሆን ምርጫው በሠላም በህዝብ ድምፅ ብቻ እንዲጠናቀቅ ማድረግ በመሆኑ አባላቱ ለዚሁ ተግተው እንዲሠሩ አቶ ገዱ አሳስበዋል፡፡
ስልጠናው በባህር ዳር ጐንደርና ደብረ ማርቆስ የተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይም በወልድያ፣ ደሴና ደብረ ብርሃን ከተሞች ይሠጣል፡፡