|
የእሣት አደጋው በንዋየ ቅድሳት ላይ ጉዳት እንዳላደረሰ ተገለፀ
|
|
በቅርቡ የእሣት ቃጠሎ አደጋ የደረሰበት የመሃል ዘጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም በንዋየ ቅድሳት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት የገዳሙ አስተዳዳሪ ገለፁ፡፡
የመሃል ዘጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም አስተዳዳሪ መምህር ሀይለገብርኤል አለሙ ለአማራ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ እንደተናገሩት በገዳሙ ላይ የካቲት 5/2002 ዓ.ም ምክንያቱ ባልታወቀ የእሣት ቃጠሎ ደርሶበታል፡፡ በነዋየ ቅድሳቱ ላይ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም፡፡
በዘጌ ከሚገኙት 7 አብያተ ክርስትያናት በ13ኛው ክፍለ ዘመን የታነፀው ገዳሙ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ይጐበኙታል ያሉት መምህር ሀይለገብርአል የደረሠው የእሳት ቃጠሎ የቱሪዝም ፍሠቱን ሊገታው እንደማይችል ገልፀዋል፡፡
መምህር ሃይለ ገብርኤል አክለውም የእሳት ቃጠሎው በደረሰበት ወቅት የምዕራብ ጐጃምና የአዊ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ በርናባስና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አያሌው ጐበዜ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በቦታው ተገኝተው ሁኔታውን በመመልከት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ገዳሙን ለማነፅ በሚደረገው እንቅስቃሴም ህዝቡ አቅሙ በፈቀደው መጠን እንዲረዳቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል ምርምራ የስራ ሂደት ሃላፊ ኢንስፔክተር ውበቱ አለ እንደገለፁት በገዳሙ ላይ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ እለታዊ መገልገያ ከሆኑት ውጭ በንዋያተ ቅድሳቱ ላይ ምንም ጉዳት አላደረሰም፡፡
የቃጠሎው መነሻ እየተጣራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኢንስፔክተር ውበቱ ሌሎች መሠል ገዳማትናም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን ባልደረባችን ዘላለም ጌታነህ ዘግቧል፡፡